ማይግሬን ምንድን ነው?
ማይግሬን
ማይግሬን ምንድን ነው?
ማይግሬን ከፍተኛ እና በተደጋጋሚ የሚከሰት ራስ ምታት ሲሆን የተለያዩ ምክንያቶችን ተከትሎ የሚነሳ እና እነዚህ ምክንያቶች ሲወገዱ ደግሞ የሚቀንስ በሽታ ነው፡፡ ህመሙ የሚከሰተው አእምሯችን ውስጥ ከሚገኙ የተለያዩ የደም ስሮች መካከል ተለቅ የሚሉት ሲያብጡና ሲሰፉ ነው፡፡ የነዚህ የደም ስሮች እብጠት በዙሪያቸው ከሚገኙ ነርቮች የተለያዩ ንጥረ ነገሮች እንዲለቁቀ ያደርጋል፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ እነዚህ የተመረቱ ንጥረ ነገሮች አእምሮአችን ለህመም ያለውን ስሜት ከፍ ያደርጉታል፡፡ በመሆኑም ለትንሽ የህመም መንስኤ ከፍተኛ የህመም ስሜት እንዲሰማ ያደርጋሉ፡፡በዚህ የሚመጣ ህመምም ወጋ ወጋ የሚያደርግ አይነት ነው፡፡
ይህ በሽታ ከ40 አመት በፊት ይጀምር እና ከ60 በላይ ሲሆኑ በተለይ በሴቶች ዘንድ ይቀንሳሉ እስከመጥፋትም ይደርሳል፡፡ በዚህ በሽታ ህፃናት ተጠቂ ሊሆኑ ቢችሉም በብዛት ግን አይታይባቸውም፡፡ምንም እንኳን ፈውስ የሌለው በሽታ ቢሆንም በተለያዩ መድሃኒቶች እና የአኗኗር ዘይቤዎች ልትቆጣጠረው ትችላለህ፡፡
የማይግሬን ምልክቶች ምንድናቸው?
ከፍተኛ የሆነ በተደጋጋሚ የሚነሳ እና በመሃል እረፍት የሚሰጥ አይነት የራስ ምታት የመጀመሪያው ምልክት ነው፡፡ህመሙ ቀስ በቀስ የሚጨምር ሲሆን ከእቅልፍህ ስትነሳ እያመመህ ከሆነ ግን ከፍተኛው የህመም ደረጃ ላይ ልታገኘው ትችላለህ፡፡
በጭንቅላትህ ግማሽ ክፍል ብቻ የሚኖር ህመም የተለመደ መገለጫው ሲሆን ከግራ ወደቀኝ (ወይም በተቃራኒው) እያለ በተለያየ ጊዜ የተለያየ ክፍልን ሊያጠቃ ይችላል፡፡ ህመሙ ከአራት ሰአት እስከ ሁለት እና ሶስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን ከጭንቅላት እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ ይባባሳል፡፡ ሰውነትህን ሁሉ ከመክበድ ባለፈ ሊያስመልስህም ይችላል፡፡ በተጨማሪም ለሽታዎች፣ ለድምፅ እና ለብርሃን ያለህን ስሜት ይጨምራል፡፡
ህፃናት ላይም ተመሳሳይ ምልክቶች ሲኖረው የሚቆይበት ጊዜ ግን አጠር ይላል ይህም ከግማሽ ሰአት እስከ አንድ ቀን ቢሆን ነው፡፡
ራስ ምታቱ ከመምጣቱ አስቀድሞ የሚታዩ ምልክቶች አሉ፡፡ እነዚህ ምልክቶች ሁሉም ህመምተኞች ላይ የሚከሰቱ ባይሆኑም ለሚታዩባቸው ሰዎች ግን ማይግሬን ሊነሳባቸው እንደሆነ ጥሩ ማመላከቻዎች ናቸው፡፡ በአማካይ ከአንድ ቀን በፊት በጣም ንቁ የመሆን በአንዳንዶች ላይ ደግሞ ቶሎ የመድከም ፣ የመናደድ፣ ጣፋጭ ምግቦችን የመፈለግ እና የመሳሰሉ ባህሪዎችን ያሳያሉ፡፡ የአይን ብዥታ፣ የእጅ ጣት መጠዝጠዝና መደንዘን፣ የንግግር መጓተት የመሳሰሉት ምልክቶች ማይግሬን ከመምጣቱ ከጥቂት ደቂቃወች በፊት ይታያሉ፡፡ እነዚህ ምልክቶች ከታዪ በኋላ ማይግሬን ሊከተል ወይም ደግሞ ምንም እንኳን ያልተለመደ ቢሆንም ማይግሬኑ ላይከሰትም ይችላል፡፡
አንዳድ ሰዎች ራስ ምታቱ ሊነሳ እንደሆነ አስቀድመው ያውቃሉ፡፡ ማይግሬኑ ከሄደ በኋላም ድካም፣ ቶሎ መናደድ፣ መደበት ብሎም የተለያዩ የቆዳ ክፍሎችህን መበለዝ ልታስተውል ትችላለህ፡፡
የማይግሬን መንስኤዎች ምንድን ናቸው?
ከ 50% በላይ የሚሆኑ በማይግሬን የተያዙ ህመምተኞች ከቤተሰባቸው ይወርሱታል፡፡ ስለዚህ በቤተሰብሽ ውስጥ የማይግሬን በሽተኛ ካለ በተለይ ደግሞ እናት፣አባት፣እህት፣ወንድም በዚህ በሽታ ተጠቂ ከሆኑ አንቺም በበሽታው ተጠቂ የመሆን እድልሽ ይጨምራል፡፡ በሽታው ከተለያዩ ሆርሞኖች ጋር ተያያዥነት ስላለው ሴት መሆን በራሱም በበሽታው የመጠቃት እድልን በትንሹ ይጨምራል፡፡
ማይግሬንን የሚቀሰቅሱ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
የተለያዩ በሽታዎች በተለያዩ ምክንያቶች እንደሚነሱ ሁሉ ማይግሬንም የራሱ ቀስቃሽ ምክንያቶች አሉት፡፡ ከነዚህ መካከል ብዙ ጊዜ የሚጠቀሰው ጭንቀት ነው፡፡ ጭንቀት በራሱ ራስ ምታትን የሚያመጣ ሲሆን ማይግሬን ላለበት ሰው ግን ዋና ቀስቃሹ ነው፡፡
ረሃብ፣ የፈሳሽ ምግብ ብቻ ተመጋቢ መሆን ወይም የተዘበራረቀ የምግብ ፕሮግራም በሽታውን ሊያባብሱ ይችላሉ፡፡ አልኮል መጠጦች፣ ኮምጣጣ ምግቦች፣ ቸኮሌት እና ቺዝ የመሳሰሉ ምግቦች በሽታንውን ያሰነሳሉ፡፡ ብዙ ወይም ትንሸ እንቅልፍ፣ የአየር ሙቀት ለውጦች፣ ሀይለኛ ሽታ፣ፀሃይ፣ ከፍተኛ ድምፆች በሽታውን ከሚያስነሱ ምክንያቶች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
በሴቶች በኩል ደግሞ የወር አበባ ኡደትን ተከትለው የሚጨምሩ እና የሚቀንሱ የሴት ሆርሞኖች ይህንን በሽታ ያባብሱታል፡፡ በተለይ የወር አበባሽ በሚመጣበት ጊዜ በሽታው ከድሮው በበለጠ ይጨምራል፡፡ ስለዚህም አንድ ሴት ስታርጥ የማይግሬን በሽታዋ ከመቀነስ አልፎ ሊጠፋም ይችላል፡፡ እርግዝናም የራሱ የሆነ ለውጥ ያስከትላል፡፡
ማይግሬንን እንዴት ልከላከል?
ማይግሬን የማይድን በሽታ ቢሆንም የሚከሰትባቸውን ጊዜያት ለመቀነስ የተለያዩ ነገሮች ማደረግ ትችያለሽ፡፡ በሽታውን ምን እንደሚያስነሳብሽ ለይተሸ ማወቅ እና ከነዚህ ነገሮች እራስሽ መጠበቅ የመጀመሪያው እና ዋናው ተግባርሽ ሊሆን ይገባል፡፡ ራስ ምታቱ በሚጀምርሽ ጊዜ መቼ እንደጀመረሽ፣ ህመሙ ሀይለኛ ወይስ ለዘብ ያለ እንደነበር፣ መድሃኒት ወስደሽ ከሆነ የወሰድሽውን መድሃኒት፣እና ሌሎች ምክንያቶችን በመፃፍ እና በተለያዩ ጊዜያት የወሰድሻቸውን ማስታወሻዎች በማመሳከር ምክንያቶቹን በቀላሉ ማወቅ ትችያለሽ፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የአኗኗር ዘይቤሽን መቃኘት ተገቢ ነው፡፡ጭንቀትን ማስወገድ፣ ምግብ በሰአቱ መብላት፣ እንቅልፍ በልኩ መተኛት፣ አልኮል መጠጦችን ማስወገድ እና ከላይ የተጠቀሱ ምግቦችን ባለመብላት ራስ ምታቱን መቀነስ ትችያለሽ፡፡ የተለያዩ ረጋ ያሉ የሰውነት እንቅስቃሴዎችን መስራት እና እራስን ከማዝናናት በተጨማሪ ደረቅ መርፌ (acupuncture) መጠቀምም ሊረዳሽ ይችላል፡፡
ራስ ምታቱ ከጀመረኝ በኋላ ምን ላደርግ እችላለሁ?
አንዴ ራስ ምታቱ ከጀመረህ በኋላ መድሃኒት በመውሰድ ፀጥ እና ጨለም ያለ ቦታ ላይ እረፍት አድርግ፡፡ ቀዝቃዛ ነገር ለምሳሌ በፎጣ የተጠቀለለ በረዶ ግምባርህ ላይ ማድረግ እንዲሁም ቡና መጠጣት ሊረዳህ ይችላል፡፡
የማይግሬን ህክምና ምንድን ነው?
ምንም እኳን በሽታው የማይድን ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ብዙ መድሃኒቶች እየተፈበረኩ ሲሆን ከብቃታቸው አንፃር ስናይም በጣም ጥሩ ናቸው፡፡ አንዳዶቹ ራስ ምታቱ ከመጀመሩ በፊት የሚከላከሉ ሲሆን የተቀሩት ደግሞ ህመሙ ከጀመረ በኋላ ህመሙን የመቀነስ ስራ ይሰራሉ፡፡ ነገር ግን መድሃኒት ከመጀመርሽ በፊት ሀኪምሽን ማማከር አለብሽ፡፡
Leave a Reply
You must be logged in to post a comment.